አዲስ: የእነ ደረጀ አለሙ(22 ተከሳሾች): የእነ ሉሉ መሰለ(8 ተከሳሾች): እና የእነ ትንሳኤ በሪሶ (10 ተከሳሾች) የዛሬ ቀጠሮ ሁኔታ

Tinsae Beriso

ተከሳሾች ያለአግባብ በቀጠሮ እየተጉላሉ እንደሆነ ገለፁ

(በጌታቸው ሺፈራው)

   እነ ደረጀ አለሙ (22 ተከሳሾች)

~ ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ምስክር ይሰማል በሚል ያልተገባ ቀጠሮ እየተሰጠባቸው እንደሆነ ገልፀዋል። በእነ ደረጀ አለሙ የክስ መዝገብ የተከሰሱ እስረኞች የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት የመጨረሻ ተብሎ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው የነበር በነሃሴ 2009 ዓም የነበር ቢሆንም ምስክሩን ታልፎ ለብይን መቀጠር ሲገባቸው ተጨማሪ ሶስት ቀጠሮዎችን ያለ አግባብ እንደተቀጠረባቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ገልፀዋል።

~የፌደራል ፖሊስ በተከሳሾቹ ላይ ይቀርባል የተባለውን ምስክር አፈላልጌ አላገኘሁትም፣ በቀጣይ ቀጠሮ አፈላልጌ አመጣዋለሁ የሚል ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ልኳል። ዐቃቤ ሕግም ለፌደራል ፖሊስ ጊዜ ተሰጥቶት ምስክሩን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

~በሌላ በኩል የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ደንበኞቻቸው የተከሰሱት ዋስትና በሚያስከለክል ክስ በመሆኑ፣ በእስረኛ አያያዝ አስከፊ የሆነው ቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኙ፣ ዐቃቤ ሕግ እስካሁን ምስክሩን ማቅረብ ስላልቻለ ከአሁን በኋላም ማቅረብ እንደማይችል ስለሚያሳይ ምስክርነቱ ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው አሳስበዋል።

~ከተከሳሾች መካከል አቶ ገረመው ፈቃዱ ምስክርነት የተጀመረው የካቲት 2009 መሆኑን፣ ማዕከላዊም ያለ አግባብ 8 ወር እንዲቆዩ ተደርገው አሁንም ምስክር ይቀርባል እየተባሉ እየተጉላሉ መሆኑን ገልፀዋል።

~በዚህ መዝገብ 15ኛ ተከሳሽ አቶ ኤርጳ ዲሳሳ በህመም ምክንያት በቀጠሮዎች በተደጋጋሚ እንዳልቀረቡ ተገልፆአል። አቶ ኢርጳ በእስር ላይ በቆዩበት ሁለት አመት ውስጥ በህመም ላይ ቢሆኑም ህክምና ማግኘት አለመቻላቸውን በዛሬው ችሎት ገልፀዋል። ቤተሰብ ሊያሳክማቸው ቢፈልግም ህክምና መከልከላቸውን ገልፀዋል። 1ኛ ተከሳሽ ደረጀ አለሙ ማዕከላዊ ታስሮ በነበረበት ወቅት በማምለጡ በሌለበት ጉዳዩ እየታየ ነው።

የእነ ደረጀ አለሙን ሙሉ ክሱን ለማየት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

የእነ ደረጀ አለሙ በእንግሊዘኛ የተተረጎመ የክስ ዝርዝር ለማግኘት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

 

   ******እነሉሉ መሰለ (8 ተከሳሾች)

~” በእስር ላይ የስኳር በሽተኛ ሆኛለሁ። ይህን የሰጠኝ እስር ነው።” አቶ ሉሉ መሰለ

~”በፈጣሪ ፈቃድ የሚመጣ ነገር እንዳለ አላውቅም” ዳኛው

~በእነሉሉ መሰለ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አሁን ለብይን ተቀጥረዋል። ተከሳሾቹ ለብይን ተብለው በተደጋጋሚ የተቀጠሩ ሲሆን ለታህሳስ 13/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። የሰማያዊ ፓርቲ የአርባምንጭ አመራር የሆነው አቶ ሉሉ መሰለ የመከላከያ ምስክር ካሰሙ 8 ወር ቢያልፍም ብይን ሊሰራላቸው እንዳልቻለ ገልፆአል። አቶ ሉሉ “እኔ ከታሰርኩ በኋላ የስኳር በሽተኛ ሆኛለሁ። ይህን በሽታ የሰጠኝ እስር ነው። ከታሰርን 2 አመት ከአራት ወር ሊሆነን ነው። በእስር ላይ ለሚገኝ ሰው ከባድ ነው” ብሏል። መሃል ዳኛው በበኩላቸው “ከአቅማችን በላይ ልንሰራ አንችልም። በፈጣሪ ፈቃድ የሚመጣ ነገር እንዳለ አላውቅም” ብለዋል።

*****የእነሉሉ መሰለን የክስ ዝርዝር በፒዲኤፍ (pdf) በኢሜል አድራሻችን ethiotrialtracker@gmail.com ብትልኩልን የሽብር ክሶችን ዳታ ለመገንባት በምንጠቀምበት ዌብ ሳይታችን አርካይቭ (archive) ለማድረግ ስለሚርዳን ምስጋናችን የላቀ ነው

     

*****እነ ትንሳኤ በሪሶ (10 ተከሳሾች)

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እነ ትንሳኤ በሪሶን በቢሮ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል። ፍርድ ቤቱ መጀመርያ ዳኛ አልተሟላም በሚል በቢሮ ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ዳኞች ለሌላ መዝገብ ተሟልተው ተሰይመዋል ተብሏል።

ህዳር 8/2010 በነበረው ችሎት ተከሳሾች ብይኑ ዘገየብን በሚል ባሰሙት ቅሬታ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በፖሊስ ተይዘው እንዲወጡ ከማድረጉም ባሻገር፣ ዳኛው ለፖሊስ አዛዡ “መሳርያው ይዛችሁ የምትመጡት ምን ልታደርጉበት ነው?” ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ባለፈው ቀጠሮ በፖሊስ ተይዘው ከችሎት እንዲወጡ የተደረጉት ቴዎድሮስ አስፋው፣ ፍሬው ተክሌ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ዳንኤል ተስፋዬ እንደሆኑ ይታወሳል። እነ ትንሳኤ በሪሶ ለታህሳስ 12/2010 ዓም ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል።

 እነ ትንሳኤ በሪሶ ሙሉ ክሱን ለማየት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

እነ ትንሳኤ በእንግሊዘኛ የተተረጎመ የክስ ዝርዝር እንዲሁም የተከሳሾችን ፎቶዎች ለማግኘት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

 

Be the first to comment on "አዲስ: የእነ ደረጀ አለሙ(22 ተከሳሾች): የእነ ሉሉ መሰለ(8 ተከሳሾች): እና የእነ ትንሳኤ በሪሶ (10 ተከሳሾች) የዛሬ ቀጠሮ ሁኔታ"

Leave a comment

Your email address will not be published.


*