አዲስ: በእነ ትንሳኤ በሪሶ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

Tensae et al

የፀረ ሽብር ህጉን አንቀፅ 7(1) በመተላለፍ ክስ የተመሰረተባቸው እነ ትንሳኤ ዛሬ ብይን ተነቦላቸዋል። በአቃቤ ህግ ባቀረባቸው ምስክሮች፣ በማእከላዊ ለፖሊስ በሰጡት ቃል እና ከብሄራዊ ደህንነት እና መረጃ ቢሮ በቀረበ የስልክ ጠለፋ የተገኘ በፅሁፍ የቀረበ ሪፖርት ብይኑ መሰራቱ በችሎት ተገልፇል። አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች በተከሳሾቹ ላይ የቀረበባቸውን ክስ ስለሚያስረዳ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ተበይኗል። ተከላከሉ መባላቸውን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ ፍሬው ተክሌ “ተከላከል በመባሌ አልከፋኝም። ፍትህ የነፈጋችሁት እኔን አይደለም። ፍትህ የነፈጋችሁት የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሳ የተገደለችውን የ8 አመት ህፃንን ነው። ” ብሏል።

ዳኞቹም በብይኑ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ ነግረዋቸዋል። የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ከሚያዚያ 12 እስከ 22 ባለው ጊዜ አቅርበው እንዲያሰሙ ታዘዋል። ከአራት ወር በላይ የቀጠሮ ጊዜ ሲሰጣቸው በጣም እንደራቀባቸው፣ ከታሰሩ ረጅም ጊዜ መሆኑን እና ተገቢ አለመሆኑን የተከሳሽ ጠበቆች ተናገረዋል። በመዝገቡ አራተኛ ተከሳሽ የሆነው ቴድሮስ አስፋው “እኛ ወጣቶች ነን። የነገ ሃገር ተረካቢዎች። ጊዜያችን በከንቱ ማለፉ ሊያሳስባችሁ ይገባ ነበር። እናንተ የተሾማችሁት ፍትህ ለመስጠት ነው። ስላለባችሁ ጫና ነግራችሁን እና ያላችሁበትን መጨናነቅ ነግራችሁን የአራት ወር ቀጠሮ ከመስጠት ተጨማሪ ዳኛ እንዲሾም እና ችሎት እንዲጨመር ማድረግ ትችላላችሁ። የተቀመጣችሁበት ቦታ ፍትህ የሚሰጡ ሰዎች የሚቀመጡበት ነው። ፍትህ የማትሰጡ ከሆነ ለምን ተቀመጣችሁ?” ብሏል። ዳኞችም በቀጠሮው ላይ ምንም ለውጥ ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

 የእነ ትንሳኤ በሪሶ ሙሉ ክሱን ለማየት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

እነ ትንሳኤ በእንግሊዘኛ የተተረጎመ የክስ ዝርዝር እንዲሁም የተከሳሾችን ፎቶዎች ለማግኘት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

Be the first to comment on "አዲስ: በእነ ትንሳኤ በሪሶ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ"

Leave a comment

Your email address will not be published.


*