አዲስ: በቂሊንጦ ቃጠሎ የተጠረጠሩ 38 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። (እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ)

Masresha Sete

 

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገው ቀደም ብሎ የተያዘላቸው ቀጠሮ ሳይደርስ ነው። ተከሳሾቹ ተፈፀመብን ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያጣራ የታዘዘው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት ላይ ያላቸውን አስተያየት ለመቀበል በማለት ፍርድቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ዳኞች አሳውቀዋቸዋል። ከዛሬው ቀጠሮ በፊትም ኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ለተከሳሾች መድረሱን ተከሳሾችን እና ጠበቆቻቸውን በመጠየቅ ዳኞች አረጋግጠዋል።

ሪፖርቱ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት መነካካት እንጂ በሙሉ የደረሰባቸውን ጉዳት እና ደርሶብናል ብለው ያመለከቱትን በደል ሁሉ እንዳላካተተ፣ አቃቤ ህግ በምስክርነት ያቀረባቸው እስረኞችም በግዴታ እና ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ በመሆኑ የእነሱም ጉዳይ እንዲጣራ እንደሚፈልጉ፣ የመብት ጥሰቱን የፈፀሙት ከፌደራል ወንጀል ምርመራ የተውጣጡ ሆነው ሳለ ሪፖርቱ በምክረ ሃሳቡ ተፈፀመ ብሎ ያመነውን የመብት ጥሰት እንዲያጣራ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮን ማዘዙ ተገቢ እንዳልሆነ እና እንደሚቃወሙ፣ ኮሚሽኑ ደፍሮ የደረሰባቸውን አካላዊ እና ሳይኮሎጂካዊ ጉዳት በሙሉ በድጋሚ እንዲመረምር በማለት ተከሳሾቹ ያላቸውን አስተያየት በቃላቸው አቅርበዋል። ብዙ ተከሳሾች ሃሳብ እንዳላቸው እና እንዲናገሩ ጠይቀው ሃሳባቸውን በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል።

በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን አስተያያት በቃላቸው በችሎት የተናገሩትን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች አስተያየቶቻቸውን በፅሁፍ ከሚቀጥለው ቀጠሯቸው በፊት በፅህፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ ተብለዋል።

ዳኞቹ የተከሳሾቹን አስተያየት ለመስማት እንጂ በሪፖርቱ ላይ በተቀመጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና የፖውሎስ ሆስፒታል ጉዳዩን እንዲያጣሩ ማዘዛቸውን ገልፀዋል።

ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ (ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3) እንደተጠበቀ ነው።

ኮሚሽኑ ያቀረበውን 5 ገፅ ሪፖርት ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይጫኑ።

ሙሉ ክሱን (33 ገፅ) ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይጫኑ

የክሱን ፍሬ ሀሳብ በእንግሊዝኛ ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይጫኑ

Be the first to comment on "አዲስ: በቂሊንጦ ቃጠሎ የተጠረጠሩ 38 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። (እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ)"

Leave a comment

Your email address will not be published.


*